1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 30 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 30 2016

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት በፈረንሳይ ፓሪስ ማራቶን በወንድም በሴትም ድል ተቀዳጅተዋል ። ከወሳኙ ድል በኋላ አትሌቶቹን አነጋግረናል ። በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያዎች ነገና ከነገ በስትያ ይከናወናሉ ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል በተከላካይ ብርቱ ስህተት ድሉን አሳልፎ ሰጥቷል ። ባየር ሙይንሽንን ዘንድሮ ምን ነካው?

Bundesliga | 1. FC Heidenheim - Bayern München
ምስል Tom Weller/dpa/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት በፈረንሳይ ፓሪስ ማራቶን በወንድም በሴትም ድል ተቀዳጅተዋል ። ከወሳኙ ድል በኋላ አትሌቶቹን አነጋግረናል ። በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ይከናወናሉ ። ለሩብ ፍጻሜ ከደረሱት ውስጥ ሦስቱ የስፔን ቡድኖች ናቸው ። የጀርመን እና እንግሊዝ ሁለት ሁለት ቡድኖችም ለሩብ ፍጻሜው ከደረሱት ውስጥ ይገኛሉ ። ፈረንሳይ ወደ ግማሽ ፍጻሜ የማለፍ ተስፋዋ በአንድ ቡድን ብቻ ተወስኗል ። ባየር ሙይንሽንን ምን ነካው? ከታችኛው ዲቪዚዮን ዘንድሮ ወደ ቡንደስሊጋው በመጣው ቡድን ተሸንፎ የደጋፊዎቹን አንገት አሰብሯል ። ሽንፈቱ ለባዬር ሌቨርኩሰን የዋንጫ ግስጋሴ መልካም ዕድል ፈጥሯል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል በተከላካይ ብርቱ ስህተት ድሉን አሳልፎ ሰጥቷል ።

በፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል መሪነቱን ከእጁ አስወጥቷል 

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ኦልድ ትራፎርድ ትናንት በደጋፊዎች ስትናጥ አምሽታለች ።  ሊቨርፑል በሉዊስ ዲያዝ 23ኛ ደቂቃ ላይ በተቆጠረ ግብ ሲመራ ቆይቶ ነበር የመጀመሪያ አጋማሽ የተጠናቀቀው ። እንደ አያያዙ ከሆነ ብዙዎች የትናንቱን ጨዋታ ሊቨርፑል አሸንፎ ከአርሰናል በ2 ነጥብ ርቀት በዋንጫ ግስጋሴው ይገፋበታል ብለው ገምተው ነበር ። ከረፍት መልስ ግን በተከላካዩ ብርቱ ስህተት ሊቨርፑል ይህን የማሸነፍ እድሉ ከእጁ አፈትልኮ ወጥቷል ። 

50ኛው ደቂቃ ላይ ብሩኖ ፈርናንዴሽ ድንገት የሊቨርፑል ደጋፊዎችን ልብ ቀጥ አድርጓል ። ኳንሳስ ለመሀል ተከላካዩ ቫን ዳይክ በተልመሸመሸ መልኩ አቀብላለው ያለው ኳስ በቀጥታ ያረፈው አድብቶ ሲጠብቅ የነበረው ብሩኖ እግር ላይ ነበር ። የግብ ጠባቂው ከግብ ክሉ ውጪ መሆኑን የተመለከተው ብሩኖ ፈርናንዴሽ ግብ ጠባቂውን አንጠራርቶ በድንቅ ሁኔታ ኳሷን ከመረብ በማሳረፍ የሊቨርፑል የድል ግስጋሴ ላይ ቀዝቃዛ ውኃ ቸልሷል ።

እንደውም 67ኛው ደቂቃ ላይ በኮቢ ማይኖ ግሩም ግብ መሪነቱን የጨበጠው ማንቸስተር ዩናይትድ ሊቨርፑሎችን አስጨንቆ ቆይቷል ። ብዙም በመከላከሉ ላይ በማተኮሩም በደረሰበት ጫና የተገኘችውን ፍጹም ቅጣት ምት ሞሀመድ ሳላኅ 84ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂውን በተቃራኒ አቅጣጫ በመላክ አቻ የምታደርገውን ግብ አስቆጥሯል ። የመጋቢት 23 ቀን 2016 የስፖርት መሰናዶ

ሞሀመድ ሳላኅ 84ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂውን በተቃራኒ አቅጣጫ በመላክ ሊቨርፑልን አቻ የምታደርገውን ግብ በፍጹም ቅጣት ምት ካስቆጠረ በኋላምስል Dave Thompson/AP/picture alliance

በዚህም መሠረት፦ ባለፈው ግጥሚያ ከማንቸስተር ሲቲ ጋ ያለምንም ግብ የተለያየው አርሰናል ከሊቨርፑል እኩል 71 ነጥብ ሰብስቦ በግብ ክፍያ ልዩነት የፕሬሚየር ሊጉ መሪነቱን ተረክቧል ።  ማንቸስተር ሲቲ በ70 ነጥብ ሦስተኛ ነው ። ሉቶን ታወን፤ በርንሌይ እና ሼፊልድ ዩናይትድ ከ18ኛ እስከ 20 ደረጃ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ይገኛሉ ።

በ60 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሀም ሆትስፐር ትናንት ኖቲንግሀም ፎረስትን 3 ለ1 ድል አድርጓል ። ቸልሲ ከሼፊልድ ዩናይትድ ጋ ሁለት እኩል ተለያይቷል ። ቅዳሜ ዕለት አርሰናል ብራይተንን 3 ለ0 ድል ሲያደርግ፤ ማንቸስተር ሲቲ ክሪስታል ፓላስን 4 ለ2 አሸንፏል ። ሉቶን ታወን በርመስን እንዲሁም ዌስትሀም ዩናይትድ ዎልቭስን 2 ለ1፤ ኒውካስል ፉልሀምን እንዲሁም ኤቨርተን በርንሌይን 1 ለ0 አሸንፈዋል ። አስቶን ቪላ ከብሬንትፎርድ ጋ ሦስት እኩል ተለያይቷል ።

በቡንደስሊጋው ባዬርን ሙይንሽን ምን ነካው?

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የበርካታ ጊዜያት የዋንጫ ባለድሉ ባዬርን ሙይንሽን ዘንድሮ ከታችናው ዲቪዚዮን ባደገው ሐይደንሀይም ቡድን መሸነፉ በርካቶችን አስደምሟል ። 2 ለ0 ሲመራ ቆይቶ የማታ ማታ የ3 ለ2 ሽንፈትን ያስተናገደው ባዬርን ሙይንሽን አሰልጣንኝ ቶማስ ቱኁል ጉዳይም አጠያያቂ ሆኗል ። አሰልጣኙ ከባዬርን ሙይንሽን መሰናበታቸው የማይቀር መሆኑ ቀደም ሲል ተነግሯል ። አሁን እስከ ዘንድሮ የቡንደስ ሊጋ ፍጻሜ ድረስስ ይቆያሉ ወይ የሚል ጥያቄ አጭሯል ።

ሽንፈት የደጋገሙት የባዬርን ሙይንሽን አሰልጣንኝ ቶማስ ቱኁል ጉዳይ አጠያያቂ ሆኗልምስል Tom Weller/dpa/picture alliance

ቅዳሜ ዕለት ዑኒዮን ቤርሊንን 1 ለ0 ያሸነፈው ባዬርን ሌቨርኩሰን አሁን በ76 ነጥብ የቡንደስ ሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ ቁንጮ ላይ ሰፍሯል ። ባዬርን ሙይንሽን በ16 ነጥብ ተበልጦ ሁለተኛ ነው ። ተመሳሳይ 60 ነጥብ ሰብስቦ በግብ ክፍያ ብቻ በመበለጥ 3ና ደረጃ ላይ የሚገኘው ሽቱትጋርት ቦሩስያ ዶርትሙንድን 1 ለ0 አሸንፏል ። እንደ ቦሩስያ ዶርትሙንድ 53 ነጥብ ሰብስቦ በግብ ክፍያ ግን 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕትሲሽ ፍራይቡርግን በገዛ ሜዳው 4 ለ1 ኩም አድርጓል ። ቮልፍስቡርግ ትናንት በቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ የ3 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ። ኮሎኝ ቦሁምን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ማይንትስ ዳርምሽታድትን 4 ለ0 ጉድ አድርጓል ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከቬርደር ብሬመንን አንድ እኩል ተለያይቷል ። ማይንትስ ወራጅ ቃጣና ጠርዝ ላይ፤ ኮሎኝ እና ዳርምሽታድት 17ኛ እና 18ኛ ቁልቁል ይገኛሉ ። የመጋቢት 16 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም ድል የተቀዳጁበት የፓሪስ ማራቶን   

አድማጮች፦ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ትንታኔ ከማለፋችን በፊት ደግሞ የአትሌቲክስ ድል ዘገባ እናስደምጣችሁ ። ትናንት በፈረንሳይ ዋና ከተማ በተከናወነው የፓሪስ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም ድል ተቀዳጅተዋል። በወንዶች ፉክክር ሙሉጌታ ዑሙ (2:05:33) 1ኛ ወጥቷል ። በሴቶች ፉክክር ደግሞ መስታወት ፍቅር (2:20:45) እና እናት ጥሩሰው (2:20:48) 1ኛ እና 2ኛ ወጥተዋል ። ውድድሩን በስፍራው ተገኝታ የተከታተለችው የፓሪስ ዘጋቢያችን ሐይማኖት ጥሩነህ ለድል የበቁት አትሌቶቻችን አነጋግራለች ።

በወንዶች ፉክክር ሙሉጌታ ዑሙ (2:05:33) 1ኛ ወጥቷልምስል Haimanot Tiruneh/DW

የማራቶን ሩጫ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች

ከፓሪስ ማራቶን ድል ባሻገር፦ ኢትዮጵያውያንአትሌቶች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተከናወኑ የአትሌቲክስ ፉክክሮች ድል ተቀዳጅተዋል ። በደቡብ ኮሪያ ዳጉ ማራቶን በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵዊቷ አትሌት ሩቲ አጋ (2:21:08) 1ኛ ወጥታለች ። በወንዶች ኬንያውያን አሸንፈዋል ። በጣሊያን ሚላኖ ማራቶንም በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵውያኑ አትሌቶች ትእግስት ዓለሙ (2:26:32) እና ፋንቱ ሹጊ (2:30:52) 1ኛ እና 3ኛ በመግባት ድል ተቀዳጅተዋል ።  በዚህም ፉክክር በወንዶች ኬንያውያን አሸንፈዋል ።  አውስትራሊያ ውስጥ በተኪያሄደው የሊንዝ ማራቶን ኢትዮጵያዊው አትሌት ደጀኔ ደበላ (2:08:33) 3ና ደረጃ ሲያገኝ፤ የኤርትራው ሯጭ ጎይቶም ክፍሌ (2:08:11) 1ኛ ወጥቷል ።  የ2ኛ ደረጃውን ኬኒያዊው አትሌት ዴኒስ ኪፕንጌኖ (2:08:24) አግኝቷል ።  ኬንያውያን ባሸነፉበት በዚሁ ውድድር በሴቶች ዘርፍ፦ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉሉሜ ተክሌ (2:34:08) 3ኛ ወጥታለች ። 

የግማሽ ማራቶን ሩጫ ውጤቶች

በግማሽ ማራቶን ፉክክሮችም በተለይ በሴቶች ዘርፍ ኢትዮጵያውያን ድል ተቀዳጅተዋል ። ጀርመን ውስጥ በተከናወነው ፈጣኑ የቤርሊን ግማሽ ማራቶን ፉክክር ለጀርመን የምትሮጠው ትውልደ ኢትዮጵያ ጀርመናዊቷ አትሌት ሜላት ቀጀልቻ ( 1:07:26) በመሮጥ 3ኛ ወጥታለች ። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ሙሉዋት ተክሌ (66:53) በመሮጥ 1ኛ፤ ዘራይ ፍታዊ ደግሞ (67:22) 2ኛ ደረጃ አግኝተዋል ። በቼክ ሪፐብሊኩ የፕራኅ ግማሽ ማራቶን በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጌጤ ዓለማየሁ (1:08:10) ሮጣ በማጠናቀቅ 1ኛ ወጥታለች ። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ንግሥት ሐፍቱ (1:09:30) በመሮች የ3ኛ ደረጃ አግኝታለች ። በወንዶቹ ድሉ የ,ኬንያውያን ሆኗል ። በስፔን ማድሪድ ፉክክርም በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ አበራሽ ሽሊማ (1:08:31) አሸንፋለች ። በወንዶች የኬንያ እና ኡጋንዳ አትሌቶች ተከታትለው በመግባት ለድል በቅተዋል ። በቻይና የሆሊ ሲቲ ግማሽ ማራቶን (1:10:17) ሮጣ ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት  ብርሃን ገ7ጊዮርጊስ 3ኛ ደረጃ አግኝታለች ።  የመጋቢት 9 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ተጋጣሚ ቡድኖችን ለመለየት ጣ ሲወጣ ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Martial Trezzini/KEYSTONE/dpa/picture alliance

የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች

በሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ነገ እና ከነገ በስትያ አራት ፍልሚያዎች ይኖራሉ ። ማክሰኞ ሚያዝያ 1 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ከእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ጋ ይጋጠማል ። በተመሳሳይ ከምሽቱ አራት ሰአት ላይ ሌላኛው የእንግሊዝ ቡድን አርሰናል የጀርመኑ ባዬር ሙይንሽንን ይፋለማል ።  በነጋታው ረቡዕ ማታም በተመሳሳይ ሰአት ሁለት ጨዋታዎች ይኖራሉ ። የፈረንሳዩ ፓሪ ሳን ጃርሞ የስፔኑ ባርሴሎናንን ያስተናግዳል ።  የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ኤስታዲዮ ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም ይፋለማል ። 

ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ በነበሩ ግጥሚያዎች እንደ አትሌቲኮ ማድሪድ አሰልጣኝነታቸው ለ100ኛ ጊዜ ብቅ ያሉት ዲዬጎ ሲሞኔ በሩብ ፍጻሜው የመጀመሪያ ግጥሚያ ተጨማሪ ታሪክ ለማስመዝገብ ተዘጋጅተዋል ። የ53 ዓመቱ አሰልጣኝ እስካሁን 49 ውድድሮች ላይ ድል አስመዝግበዋል ። ረቡዕ ከተሳካላቸው 50ኛ ድላቸው ሆኖ ይመዘገባል ። የመጋቢት 2 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ የ64 ዓመቱ ካርሎ አንቼሎቲ ምስል Adam Davy/PA Wire/dpa/picture alliance

ከ50 በላይ ድሎችን ማስመዝገብ የቻሉ አሰልጣኞች

 እስካሁን ከ50 በላይ ድሎችን ማስመዝገብ የቻሉ አሰልጣኞች ስምንት ናቸው ። ካርሎ አንቼሎቲ ላይ የተጠጉት የቸልሲው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ናቸው ። እስካሁን 109 ጊዜ አሸንፈዋል ። የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ የ64 ዓመቱ ካርሎ አንቼሎቲ 114 ድሎችን በማስመዝገብ ቀዳሚ ናቸው ። የማንቸስተር ዩናይትድ የረዥም ዘመን አሰልጣኝ የ82 ዓመቱ ጡረተኛ ሠር አሌክስ ፈርግሰን በ102 ድሎች 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። አርሰናልን ለረዥም ዘመን ያሰለጠኑት ሌላኛው የ74 ዓመት ጡረተኛ አርሰን ቬንገር  82 ጊዜ አሸንፈዋል ። የኤኤስ ሮማ አሰልጣኝ የ61 ዓመቱ ሆዜ ሞሪኞ 77 ጊዜ በማሸነፍ አርሰን ቬንገርን ተከትለው 5ኛ ደረጃ ላይ ሠፍረዋል ። የ72 ዓመቱ የኔዘርላንድ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አሰልጣኝ ሉዊ ቫንጋል በ95 ጨዋታዎች 57 ጊዜ ድል በመቀዳጀት 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። የ56 ዓመቱ የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ እስካሁን በ100 ጨዋታዎች 56 ጊዜ በማሸነፍ 7ኛ ደረጃውን ተቆናጠዋል ። ዘንድሮ በፕሬሚየር ሊጉ ዋንጫ የማንሳት እድላቸው ከፍተኛ ከሆኑ ሦስት አሰልጣኞች መካከልም ይገኛሉ ። የ63 ዓመቱ የቀድሞ የሊቨርፑል ሌላኛው አሰልጣኝ ራፋኤል ቤኒቴዝ በበኩላቸው በ95 ጨዋታዎች 53 ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW