1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ጨዋታዎች ተጨማሪ ወርቅ አገኘች

ረቡዕ፣ መጋቢት 11 2016

ጋና አክራ ውስጥ በሚከናወነው የአፍሪቃ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ቡድን እንደተጠበቀው ተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያ አገኘ ። ዛሬ ጠዋት በተከናወነው የ20 ኪሎ ሜትር የወንዶች የርምጃ ፉክክር በአትሌት ምስጋና ዋቁማ ኢትዮጵያ ወርቅ አግኝታለች ። በተመሳሳይ የሴቶች የርምጃ ፉክክር በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ስንታየሁ ማስሬ የብር ሜዳልያ ተገኝቷል ።

ለኢትዮጵያ በ800 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው አትሌት ሴቶች ጽጌ ዱጉማ
ጋና አክራ ውስጥ በሚካሄደው የአፍሪቃ ጨዋታዎች ለኢትዮጵያ በ800 ሜትር የሩጫ ፉክክር የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው አትሌት ሴቶች ጽጌ ዱጉማ ። ውድድሯን በአንደኛነት ያጠናቀቀችው በ1:57.73 በመሮጥ ነውምስል Äthiopischer Leichtathletikverband

ጋና አክራ ውስጥ በሚከናወነው የአፍሪቃ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ቡድን እንደተጠበቀው ተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያ አገኘ ። ዛሬ ጠዋት በተከናወነው የ20 ኪሎ ሜትር  የወንዶች የርምጃ ፉክክር በአትሌት ምስጋና ዋቁማ ኢትዮጵያ ወርቅ አግኝታለች ። በተመሳሳይ የሴቶች የርምጃ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ስንታየሁ ማስሬ ብር ሜዳልያ  አስገኝታለች ።ዛሬ የተገኙትን ሜዳሊያዎች ጨምሮ ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ደረጃዋ ወደ 10ኛ ከፍ ብሏል ።  እስከ ሰኞ ከሰአት ድረስ የኢትዮጵያ ቡድን በሜዳሊያ ሰንጠረዥ 26ኛ ነበር ።  

ከኢትዮጵያ ቡድን ከበላይ ሞሮኮ በአምስት ወርቅ፤ ኤርትራ በስድስት ወርቅ 9ኛ እና 8ኛ ላይ ይገኛሉ ።  የኢትዮጵያ ቡድን እስካሁን አምስት የወርቅ፤ 3 የብር እና 1 የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል ። የወርቅ ሜዳሊያ በተጨማሪ ያስገኙት፦ ንብረት መላክ በ10,000 ሜትር ወንዶች፤ በ3000 ሜትር መሰናከል ወንዶች ፉክክር ፍሬው ደቢሳ ናቸው ። በሴቶች የ5000 ሜትር ፉክክር መዲና ኢሳ እና በሴቶች 800 ሜትር ጽጌ ዱጉማ ተጨማሪ ወርቅ  አስገኝተዋል ። 

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በጋና አክራ ለውድድር ተዘጋጅተውምስል Äthiopischer Leichtathletikverband

የኢትዮጵያ ቡድን ዛሬ ከሰአት በሚኖረው የሴቶች የጦር ውርወራ የፍጻሜ ፉክክር አትሌት የሺወርቅ አንማው እና ድንገቴ አዶላን ለተጨማሪ ሜዳሊያ ያወዳድራል ። ከሰአት በሚኖረው የ3000 ሜትር የሴቶች መሰናከል ሩጫ ውድድርም አትሌት ዓለማየሁ ወለተጂ፤ አትሌት ሎሚ ሙለታ እና አትሌት ፍሬሕይወት ገሠሠ ለሜዳሊያ ይጠበቃሉ ።  ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ኬቻማን ዖጁሉ እና በቀለ ጂሎ የሚፎካከሩበት የሦስት ጊዜ መስፈንጠር ዝላይ የፍጻሜ ፉክክርም ዛሬ ከሰአት ይካሄዳል ። በወንዶች 800 ሜትር የፍጻሜ ፉክክር አትሌት ዮሐንስ ተፈራ ዛሬ ከሰአት ለሜዳሊያ ይፎካከራል ። የሴቶች እና የወንዶች የአራት አትሌቶች የ100 ሜትር የዱላ ቅብብል ፉክክርም ዛሬ ይከናወናል ።  በ400 ሜትር የተሳተፈው የወንዶች ቡድን ከግማሽ ፍጻሜው ውድድር ማለፍ ሳይችል ቀርቷል ።  የመጋቢት 9 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ዘንድሮ የአፍሪቃ ጨዋታዎች የሚካሄድባት የጋና ዋና ከተማ አክራ በከፊልምስል Imago/UIG/T. Beddow

ሁለተኛ ሳምንቱን ባስቆጠረው እና የተለያዩ የስፖርት ዘርፎችን በሚያካትተው የአፍሪቃ ጨዋታዎች ግብጽ አሁንም በበላይነት ትመራለች ። ግብጽ እስካሁን 92 የወርቅ፤ 40 የብር እና 33 የነሐስ በድምሩ 165 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች ። ናይጄሪያ 31 የወርቅ፤ 22 የብር እንዲሁም 32 የነሐስ በድምሩ 85 ሜዳሊያዎችን ሰብስባ የሁለተኛ ደረጃ ይዛለች ። ደቡብ አፍሪቃ በ27 የወርቅ፤ በ29 የብር እና በ38 የነሐስ በድምሩ 94 ሜዳሊያ የሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ። 

የኤርትራ ቡድን 6 የወርቅ፤ 2 የብር እና 5 የነሐስ በድምሩ 13ሜዳሊያዎችን ሰብስቦ ከአንድ እስከ ዐሥር ካሉት ሃገራት ተርታ በመሰለፍ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። የፊታችን ቅዳሜ በሚጠናቀቀው የአፍሪቃ ጨዋታዎች፦ እግር ኳስ፤ የእጅ ኳስ፤ ነጻ ትግል፤ ባድሜንተን፤ የውኃ ዋና፤ ጁዶ፤ ቴኳንዶ፤ ብስክሌት፤ ቴኒስን ጨምሮ በ23 የስፖርት ዘርፎች ግጥሚያዎች ይኖራሉ ።   

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW